እግዚአብሔርን አጥብቆ መታመን እግዚአብሔርን ለሰዎች የምናስተዋውቅበት ሁነኛ መንገድ ነው

Reading Time: 5 minutes

አንድ ሰሞን አዲስ አበባ የኦሎምፕያ መንገድ አካባቢ የተለጠፈ የአንድ ድርጅት የማስታወቂያ ሰሌዳ “ማየት ማመን ነው” ይል ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ክርስትና “ማመን ማየት ነው” የሚል መለዮ ያለው ይመስላል። ኢየሱስ ከሙታን ሲነሳ የዛሬ ሁለት ሺህ አመት ተገኝተን በአይናችን አላየንም: አልያም ከሙታን ሲነሳ የሚያስቃኝ በቪድዮ ተቀርጾ የተቀመጠልን ማስረጃ የለም። ነገር ግን በእምነት ሰው አይቶ ሊያምን ከሚችለው በላይ ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሳው አምነን እርግጠኞች ሆነናል። በተጨማሪም ኢየሱስ “ትንሳኤና ህይወት እኔ ነኝ: የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ህያው ይሆናል” ያለውን አሜን ብለን በእምነት ተቀበልን እንጂ ከሞትን በኋላ ስላለው ጉዳይ አንዴ ሙቼ ላረጋግጥ ብለን አይደለም ያለንን እርግጠኝነት ያገኘነው። በእውነቱ ከሆነ ስለ እምነት ይሄን እንበል እንጂ የምናምንባቸው ነገሮች ከታሪክ የተፋቱ: አየር ላይ ያሉ: የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መሰረት የሌላቸውና: በእግዚአብሔር ማንነትና ባህርይ ላይ ያልተመረኮዙ አይደሉም። የወደድነውንና የምኞታችንን ነገር እግዚአብሔር ያደርጋል ብለን ስላመንን እግዚአብሔር የማድረግ ግዴታ የለበትም። ግዴታ የለበትም ብቻ ሳይሆን አያደርገውምም።

ስለ እምነት ብዙ ሊባል: ብዙ ሊሰበክ: ብዙ ሊጻፍ የሚቻልበት ርዕስ ቢሆንም: በዚህ ጽሑፌ ግን ላስተላልፍ የወደድኩት ሃሳብ እግዚአብሔርን ምንም በማይመስል ሁኔታ እንኳን የሙጥኝ ብለን ስንታመነው እና ስናምነው እርሱን በማያውቁ ሰዎች ፊት ስለምናሰጠው ስም: ክብርና እውቅና ነው። ልሞግተውም የፈለኩት ሃሳብ እግዚአብሔርን አጥብቆ መታመን እግዚአብሔርን ለሰዎች የምናስተዋውቅበ ሁነኛ መንገድ ነው የሚል ነው

ልጅ ሆኜ በማድግበት ጊዜ: ውዷ እናቴ የትኛውም አይነት መኪና ውስጥ ጋቢና መቀመጥ እንደማትወድ ትዝ ይለኛል:: እንደው እንደ እድል ሆኖ ጋቢና ከተቀመጠች ደግሞ “ቀስ በል”: “ፈጠንክ እኮ”: ” መስመርህን ጠብቀህ ለምን አትነዳም” ወዘተ በማለት ፍቅር በሞላበት የእናትነት ለዛዋ መኪናውን ከመንዳት ባልተናነሰ ለሹፌሩ መመርያ መስጠት ታዘወትራለች። በልጅነት አእምሮዬ ግን ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር: የመኪና ዘዋሪው ዉዱ አባቴ ሲሆን ያለ ምንም ትግል ጋቢና እንደምትቀመጥና ያለ ብዙ ጭንቀት እየሳቀችና እየተጫወተች እንደምትሄድ ነው። ታድያማ ምን ገባኝ መሰላችሁ? አባቴ ጎበዝ ሹፌር መሆኑን እንደምትተማመንበት ገባኝ። እኔም የእሷን በአባቴ የአነዳድ ብቃት ላይ ያላትን መተማመን ከሁኔታዋ ተነስቼ በማጤን ብቻ: ያለ ምንም ስብከት እና ምስክርነት አባቴ ጎበዝ የመኪና ሹፌር ነው ብዬ ተቀበልኩ ማለት ነው።

ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስና አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንመልከት:: የዳንኤል መጽሐፍ እንደሚተርክልን: ኢየሩሳሌምን ከብቦ የነበረው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነፆር በአንድ ወቅት     ከፍታው ስድሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠርቶ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ ያቆመዋል። ከዚያም  ያቆመውን ምስል ታድመው ያስመርቁ ዘንድ በግዛቱ የነበሩትን  መኳንንትን፣ አገረ ገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምት ሁሉ ይጋብዛል:: ለተጋበዙትም ሰዎች አጠር ቀጠን ያለ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል:: ይህም ትዕዛዝ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ሲሰሙ፣ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው መስገድ እንዳለባቸውና፤ አይ አሻፈረኝ የሚል ካለ ደግሞ፣ ወዲያውኑ በሚንበለበል የእሳት እቶን ውስጥ የመወርወር እጣ ፈንታ እንደሚገጥመው ነው:: ይሄን ትዕዛዝ በመከተልም: የተሰበሰበው ህዝብ ሁሉ ለቆመው ምስል የተባሉትን የድምጽ አይነቶች በሰማ ጊዜ ተደፍቶ ሲሰግድ: አንዳንድ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ሰዎች ግን ንጉሱ ላቆመው የወርቅ ምስል እንዳልሰገዱ በኮከብ ቆጣሪዎች ክስ ወደ ንጉሡ ይቀርብባቸዋል:: ክሱም በዋነኝነት የተነጣጠረው: ቀደም ሲል ዳንኤል ንጉሱ ፊት ካገኘው ሞገስ የተነሳ: በዳንኤል አሳሳቢነት የባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች ተደርገው በተሾሙት በነ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ላይ ነበረ:: የቀረበባቸው ክስ ለቆመው ምስል አለመስገድ ቢሆንም አለመስገዳቸው የተሰጠው አንድምታ ግን የንጉሥን ትዕዛዝ እንደማይቀበሉና የንጉሡንም አማልክቶች እንደማያገለግሉ ስለነበር: ንጉሡን ክፉኛ ያስቆጣዋል:: ንጉሡም ክስ የቀረበባቸውን እነዚህን የዳንኤልን ጓደኞች የመጨረሻ እድል ሰጥቶ እንዲሰግዱ ሊያግባባቸው ቢሞክርም በዚህ ጉዳይ እንደ ሀገራችን ብሂል ብዙም “እንካ ሰላንትያ” እንደማያስፈልጋቸውና ንጉሡ የፈለገውን ቢያደርግ አምላካቸውን እንደሚታመኑ: ቢወድ ሊያድናቸው እንደሚችል: ደግሞም ባያድናቸውም ከእርሱ ውጪ የሚሰግዱለትም ሆነ የሚያገለግሉት አምላክ እንደማይኖር እንቅጩን ይነግሩታል:: ታሪኩን አብዛኞቻችን እንደምናውቀውም: ንጉሡ ይሄን በሰማ ጊዜ እጅግ በመቆጣት: የእቶኑ እሳት ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድድ በማዘዝ እነ ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጎ ወደዚያ እንዲጣሉ ያዛል:: 

እዚህ ጋር ቆም ብላችሁ አስቡ:: እናንተ በነሲድራቅ ቦታ ብትሆኑ ምን ታደርጋላችሁ? ሆ ሆ ስንት እርኩሰት በሚሰራበት ዘመን እቺም ሀጥያት ሆና ለዚህች ብሎ በእሳት ከመቀቀል ለአንድ ቀን ለወርቅ ምስል ብሰግድ ጌታም ይረዳኛል(ይገባዋል) ትላላችሁ? አልያም ደግሞ ለወርቁ ምስል እየሰገድን አስመስለን ግን በልባችን ለያህዌ አንድ አምላክ እንስገድ የሚል ስትራቴጂ ትቀምራላችሁ? ወይንስ እግዚአብሔር መሃሪ ነው: ሰግጄ በኋላ በንሰሃ ኃጥያቴን እታጠባለው ትላላችሁ? መልሱን ለእናንተ ልተወውና ወደነ ሲድራቅ ታሪክ ስንመለስ እነርሱ ግን እግዚአብሔርን በመታመን በአቋማቸው ስለጸኑ ሰባት እጥፍ እየነደደ ወዳለው እቶኑ እሳት ተጥለዋል:: የታመኑበትም አምላክ አብሯቸው ከመሆኑ የተነሳ እሳቱ እንኳን ሰውነታቸውን ሊጎዳ ይቅርና ከራስ ጠጉራቸውም አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች: የመጎናጸፍያቸውም መልክ እንዳልተለወጠና ጭራሽ የእሳትም ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል::

ይሄን ያየ ንጉሥም የሚከተለውን ይናገራል: 
“መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና። ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።”
ዳንኤል ፫:፳፰-፳፱

ውድ አንባብያን ሆይ: ከንጉሡ ንግግር ምን አስተዋላችሁ? ቀደም ሲል ንጉሡ ” እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ባትሰግዱ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ብሎ ተሳልቆ አልነበረምን? እነ ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎ እግዚአብሔርን የሙጥኝ ብለው በማመናቸው ምክንያት ከእጁ ሊያድናቸው የሚችለውን አምላክ በሚገባ ያስተዋወቁት አይመስላችሁም? እነ ሲድራቅ በማመናቸው ንጉሡ ማየት እና ማወቅ አልሆነለትም? እስኪ አበክረን የንጉሡን ንግግር እንቃኘው:: አንደኛ ከእጄ እናንተን ለማዳን ችሎታ ያለው የትኛው አምላክ ነው ብሎ በልበ ሙሉነት የተናገረውን ስላቃዊ ጥያቄ: ማንም ሊያሳምነው ወይም ብዙ ሊያብራራለት ሳያስፈልግ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ አምላክ” በማለት ለነ ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጎ አምላክ እውቅናን ሰጥቷል:: እውቅናን መስጠት ብቻ ሳይሆን የነ ሲድራቅንም አምላክ ባርኮኣል:: አስቡት ለአማልክቴ አትገዙም ብሎ እሳት ውስጥ የከተታቸው ሰው ተገልብጦ አምላካቸውን ሲባርክ! ሌላው የንጉሡን ትዕዛዝ የጣሱበትንም ትክክለኛ ምክንያት ኮከብ ቆጣሪዎቹ ሊሰጡት እንዳሰቡት የተንሸዋረረ ትርጓሜ ወይም ንጉሡን ስለናቁ ሳይሆን አምላካቸውን ስለታመኑ መሆኑን ንጉሡ ከንግግሩ የተረዳ ይመስላል:: በተጨማሪም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለም በማለት የነ ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጎን አምላክ ብቸኛ አዳኝነት መስክሯል:: በስተመጨረሻም የወርቁ ምስል ለጊዜውም ቢሆን ተረስቶ አሁን የሚያስቀጣው በነ ሲድራቅ አምላክ ላይ አንደበትን ማላቀቅ እንደሆነ በዚው በንጉሡ ታውጇል::

ከዚህ ታሪክ ታድያ ምን እንማራለን? እኛ እግዚአብሔርን ቢያድነንም ባያድነንም: ቢያረግልንም ባያረግልንም: ቢሞላም ቢጎድልም ከእርሱ ውጪ አምላክ የለም ብለን የሙጥኝ ስንለው በማያምኑ ሰዎች ፊት ራሱ ትልቅ ምስክርነት እንደሆነና: እግዚአብሔርን ከማስደሰት አልፈን ለሌሎች ሰዎችም ብቸኛ አዳኝነቱን: ቢታመኑበት የማያሳፍር መሆኑን: ብሩክ አምላክ መሆኑን የምናሳይ ህያው ምስክሮች እንሆናለን:: በስተመጨረሻም ቃሉ

“ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም”
(ዕብራውያን ፲፩÷፮)

እንደሚል እኛም በሙሉ ልባችን በእግዚአብሔር በመታመን ደስ ልናሰኘውና እንደ እነ ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጎ በአምላካችን ታማኝነት የማንደራደር ሰዎች እንድንሆን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን!

If you enjoyed this article, please share it to others.
Ruth Christian
Ruth Christian

5 Comments

Leave a Reply to ChanokhCancel Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

    • ሩታ: በጣም ድንቅ መልዕክት ነው!
      እምነት በተግባር ሲመሰከር ውጤቱ ቦታና ግዜ ተሻጋሪ መሆኑነ ቁልጭ አድርገሽ አሳይተሽናል።
      ህያው እግዚአብሀሔር ይባርክሽ!

  1. ሩትዬ የኛ ቅመም እሚደንቅ ድንቅ መልክት ነው!!!! በእጥፍ ተባረኪልን!!!! የእምነት ሀይል በጣም ይገርመኛል ሁሌ, እምነት ውስጥ ብዙ ያልገባን ሚስጥር እና የእምነትን ሀይል በቅጡ አልተረዳነውም!! የገባሽን እንደዚ አካፊይን ቅመምዬ!❤️🙏 ዘመንሽ ሁሉ እሱን በማወቅ እና በማገልገል ይለቅ ተባረኪልን!!!❤️‍🔥❤️‍🔥🙏🙌

  2. በጣም ድንቅ መልዕክት ሩታዬ። በወሬ እና በቃል ብቻ ሳይሆን እርሱን በመታመን ለብዙዎች ማሳየት እንደምንችል በጥሩ ቋንቋ እና በድንቅ መረዳት አሳይተሽናል። ብሩክ ሁኚ።