ብቁ ያልሆንኩበት ጉዳይ – ክፍል 1

Reading Time: 3 minutes

መንፈሳዊ ህይወት የሚገርም ነው:: 

አንዳንዴ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ አእምሮዬ ላይ የሚመጣው መንበርከክ ነው:: “አንዳንዴ” ያልኩት በስህተት አይደለም: አንባቢ ሆይ ልትፈርድብኝ አትቸኩል:: እናማ በነዚህ “አንዳንዴ” በሆኑ ቀናት ጌታዬን አመስግኜ: በሰማያት ያለችው የእርሱ ፈቃድ በዚች ውብ ዕለት ትፈጸም ዘንድ ጸሎቴን አድርሼ: ለሊቱን ሙሉ ልቤ ውስጥ ሲፈስ ያደረውን ዝማሬ እየተቀኘው ወደ ቀን ጉዳዬ አቀናለው:: እንዲህ ባሉት ቀናት: በተቻለኝ አቅምና ባገኘሁት ሰዓት መንፈስን የሚያንጽ ስብከት: መዝሙር: ምስክርነት ወዘተ ሳደምጥ እውልና: በመሸ ጊዜ ጉልበቶቼ መልሰው አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት ተንበርክከው በሰላም ላዋላቸው አምላክ ምስጋናን ያቀርባሉ:: ሊሊ እንዲህ አይነቱ የህይወትን ምዕራፍ ልትገልጽ ፈልጋ ይመስለኛል “ውሃ ውሃ እንዳይል: ህይወቴን አጣፍጠህ: ይሄ ነው ማይባል ልዩ ጣዕም ሰጥተህ” ብላ የዘመረችው:: እነዚህ “አንዳንዴ” የሆኑ ቀናት ታድያ እጅግ ቅዱስ ናቸው: ሁሉስ ተሽጦ ቢገዙ ያንስባቸዋል እንጂ መች ይበዛባቸዋል?! አቤት ይሄን መንፈሳዊ ከፍታ ስወደው! ህይወታችንን መቆጣጠር የምንችልበት ሪሞት ቢኖር ኖሮ: እዚህ ከፍታ ላይ ፖዝ አርጌ ባቆማት ምንኛ ደስ ባለኝ:: የኛ የሰው ልጆች ክፉ አባዜ ሆኖ ኖሮ: አንድ ነገር ምንም ውድ ቢሆን እጃችን ሲገባ ይቀልብናል: ስናጣው ደግሞ የዋጋውን ክቡርነት እንረዳለን:: 

እነዚህ “አንዳንዴ” የሆኑ ቀናት ሌላ ገጽታ ደግሞ አላቸው:: ያው “ሌላ ገጽታ” ያልኩት “መጥፎ ጎን” ላለማለት ብዬ ነው:: ምክንያቱም ቀኖቹ ምን አጠፉ! ለማንኛውም ስንመለስ: ሌላው ገጽታ ራሱን የሚገልጠው: ይሄ መንፈሳዊነት ከራሴ ብቃት እንደሆነ ማሰብ ስጀምር: በብቃቴም ላስቀጥለው እንደምችል በመተማመን አያሌ የመንፈሳዊ ከፍታ ቀናትን ለማሳለፍ ሳቅድ: ሳወጣና ሳወርድ ነው:: ከኔም በላይ መንፈሳዊ ሰው ያለ እስከማይመስለኝ ድረስ በጣም ጸላይ: በጣም ዘማሪ: ቤተ ክርስቲያን ሂያጅ: ቃሉን አንባቢ ወዘተ እንደሆንኩ ማሰብ ስጀምር ነው:: እውነት ለመናገር እንዲህ ብሎ ማሰብ ራሱ አይጠበቅብኝም:: በቃ የመንፈሳዊ ከፍታ ምንጩ ልዕለ ተፈጥሮኣዊ የሆነ ሃይል መሆኑን መዘንጋት ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ:: ሰዎች የትኛውንም አይነት ችግራቸውን ቢያዋዩኝ: በጸሎቴ መፍታት እንደምችል እርግጠኛ ስሆን: የእግዜር ጎረቤትና አፈ-ቀላጤ አርጌ ራሴን ማየት ስጀምር ያኔ ነገር መበላሸት ይጀምራል:: 

ከዛማ ሰይጣን ምን ሰርቶ ይብላ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መልሱ ያው የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚዞር አንበሳ ዙርያችንን ይዞራልም አይደል?! እናማ ዙርያዬ ሲያንዣብብ ይቺን ነጥብ ታህል ትምክህት ያገኝና ያቺን የትምክህት ቀዳዳ ቦርቡሮ ቦርቡሮ: ወደ ውስጥ በማጮለቅ እንዴት እንደሚፈጠፍጠኝ ያሰላልኛል:: የእግዚአብሔር ጎረቤት ነኝ ብዬ ትንሽዬ ኩፈሳ ነገር ላይ ባለሁበት ሰዓት: የሃጥያት ወጥመድ ዘርግቶልኝ ኖሮ: አስቀያሚ በሆነ መንገድ ከዛ ከ30ሺ ጫማ ከፍታ መንፈሳዊ በረራ ከብርሃን በፈጠነ ቁልቁል ይፈጠፍጠኛል:: ኤጭ!! የምር በጣም የሚያስጠላ: እጅግ የሚያናድድ ነገር! ከደቂቃዎች በፊት የከፍታ በረራ ላይ ነበርኩ: አሁን ደግሞ እንክትክቴ ወጥቶ: ወይ አልሞት ወይ አልድን በሆነ አወዳደቅ ዘጭ! መንፈሳዊው ሀሁ ራሱ እስኪጠፋብኝ ድረስ ቁልቁል ተንከባልያለው:: ነገሩ “እኔ ምን አይነት ጎስቋላ ሰው ነኝ: ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?” እንዳለው ነው ታላቁ ሓዋርያ! 

ኡፍ ምናለ በነቃሁበት: ምናለ ይሄን ክብር ባላስነካው ብዬ እርር ድብን ልል እችላለው ግን ጊዜን ወደሗላ መመለስ አይቻል ነገር! ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ወጥመድ እኮ ነው “ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ: በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ሓጥያት” ብሎ የገለጸው:: ተፈጥፍጬ ያረፍኩበት: ለጊዜው ቁልቁል ቤት እንበለውና: እንዴት እንደሚያስጠላ! የሆነ በቃ ተንቀሳቃሽ ሬሳ የሆንኩ ያክል ነው የሚሰማኝ:: ጸሎት የለ: መዝሙር የለ: ቃሉን ማጥናት የለ! ለካ ለመንበርከክም ሃይል ያስፈልግ ኖሯል ወገን! እዚህ ቁልቁል ቤት: ጸሎት ከአየር ጋር ማውራት: መዝሙር ተራ የሙዚቃና የግጥም ውህድ: ቃሉ ደግሞ የስነ-ጽሑፍ ጥርቅም የሆነ ይመስላል:: ሁሉም ጣዕም የለውም:: ለነገሩ: በምላስ ውስጥ ያሉት ህዋሳት ከሞቱ: የጣፈጠ ምግብ እንኳን ውሃ ውሃ ይል የለ! እዚህ ቁልቁል ቤትም መንፈሳዊ ህይወት ውሃ ውሃ ነው የሚለው: አንዳች ጣዕም የለውም:: ያቺ ሪሞት አሁንም ብትኖረኝና ምነው ይሄኛውን ምዕራፍ በፍጥነት ባሳለፍኩት!

አንባቢ ሆይ: አውቃለው አንዳንድ ሰባኪያን: ሁሌም መንፈሳዊ ከፍታ ላይ እንዳሉ እንደሚነግሩህ:: አንተ ብቻ ሁሌ የምትወድቅ: አንተ ብቻ የምትዝል: አንተ ብቻ “አንዳንዴ” ያልኳቸውን ቀናት አንዳንዴ እንጂ ሁልጊዜ የማትኖራቸው ለሚመስልህ: ላንተ: አዎ ላንተ ነው ይሄ ጽሑፍ:: ለዛም ነው ከመፍረድህ በፊት ታገሰኝ ያልኩህ:: ሁሌ መንፈሳዊ በረራ ላይ እንደሆኑ የሚነግሩህ ሰዎች አሉ ኣ? አጋጣሚ ሆኖ እኔ እነሱን አይደለሁም:: ብዙ ጊዜ እወድቃለው: ብዙ ጊዜም እነሳለው:: ስለዚህ እስካሁን ካሳለፍኳቸው ከነዚህ ሮለርኮስተር ከሆኑ ቀናት የተማርኩትን አንዳንድ ነገሮች ልንገርህ:: በክፍል ሁለት ጠብቀኝ የትም እንዳትሄድ አደራ!

If you enjoyed this article, please share it to others.
Ruth Christian
Ruth Christian

20 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  1. ብዙ ሰዎች የሚያሳልፉት የሕይወት ቻለንጅ ነው ስለከፈለከን ሀሳብ ተባረክ

  2. እውነት ነው ይህን እውነታ መረዳት በምንገዛው የሕይወት ጎዳናችን ላይ ለምንሄደው ወሳኝ አካሄድ ነው።
    ለምሳሌ በአየር ላይ የምበሩ አዕዋፋት ምንም በምድር ካሉ ሁሉ ላይ ከፍ ብለው ብበሩም
    ይህ ግን መኖሪያቸው አይደለም።ምክንያት ለማደር ሆነ ለማረፍ ዝቅ ብለው መወረድ አሉባቸው።
    ልክ የክርስትና ጉዞ እንደዛ ነው መውጣት ያለ እንድሁም መውረድ።

    ይህም ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ጸጋና ኃይል እንመካ ዘንድ ነው።
    ጸጋና ሰላምና ይብዛልን🙏

  3. እራሴን ያየሁበት መልክት ነው:: ተባረኪ በብዙ ደግሞ ክፍል 2 አፍጥኝው::